የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሆርን ሪቪው ጋር ኢትዮጵያ በቀጣናው ስላላት ዲፕሎማሲያዊ አቋም ሲወያዩ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስለሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድርን በተመለከተ ደግሞ የኢትዮጵያን ወቅታዊ አቋም ዳግም አስምረውበታል። ቃል አቀባዩ ባለፉት ወራት በህወሓት ጥቃት ሰለባ ለሆኑት በአፋር እና በአማራ ክልል ለሚኖሩ ዜጎች  አፋጣኝና ውጤታማ የሆነ እርዳታ በመስጠት ረገድ  መንግስት የተጋረጠበትን አንዳንድ ተግዳሮቶች በተመለከተ ገለጻ ሰጥተዋል።

ሆርን ሪቪው:

አምባሳደር፣ እኛን ለማነጋገር ጊዜ ስለሰጡን እናመሰግናለን። በሰሜን አገራችን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በአፋር እና በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣውን ግጭት እንዲሁም የመንግስትን በጣም አስፈላጊና የማይተካ ዕርዳታ ለማድረስ ያለውን ሚና ቢያብራሩልን? በተጨማሪም፣ በዚህ ጥረት የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር እየሰራ ነውን?

በሕወሃት በኩል ያገረሸው ትንኮሳና ጥቃት በንጹሃን ዜጎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እና ኑሯቸውን እያወከ ነው። መንግስት ለእርዳታ የሚሆን ገንዘብ ቢመድብም ጠላት ቡድኑ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን በግጭት ለተጎዱት የአፋር እና የአማራ ክልል ዞኖችም እንዳይደርስ ማደናቀፉን ቀጥሏል። ለእነዚህ ክልሎች ከተመደበው ገንዘብና ሀብት በተጨማሪ ተደራሽነቱ እንዲረጋገጥ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው። ይህን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው  ሲሆን የአለም አቀፉ ማህበረሰብም የሚያተኩርበትና የሚከታተለው ነው።

ኢትዮጵያዊያን እንደመሆናችን ህዝቡ ዕርዳታ ማግኘት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በዋነኛነት የሚያሳስበን የህዝባችን ህልውናና ደህንነት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ ቡድን ጥረታችንን እያደናቀፈ እና እያገደ ነው። የዕርዳታው መድረስ የሚረጋገጠው በግጭት ወደተጎዱ አካባቢዎች መሄድ ሲቻል ብቻ ነው። በተጨባጭ የሚታዩትን እውነታዎች በሙሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀቁን ግን መካድ የለብንም፡፡ አካፋን አካፋ ማለት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይሄ ሀቅ በደንብ መታወቅ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ መወገዝም  ያለበት ነው።

እንደ የዓለም የምግብ ፕሮግራም/ WFP ካሉ አለም አቀፍ አጋሮች ጋር እየሠራን ነው። ነገር ግን የአማራና የአፋር ክልሎች በሕወሃት ወረራ ክፉኛ የተጠቁ በመሆናቸው አጋሮቻችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በነዚህ ክልሎች በሚገኙ መዳረሻዎች ላይ የሚደረገውን የዕርዳታ አቅርቦት የበለጠ ትኩረት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። ምንም እንኳን በዕርዳታ መገኘትና እና በአቅርቦት ላይ አንዳንድ ክፍተቶች ባይታጡም፣ በተጨባጭ ባለው አስቸኳይ ፍላጎት እና አሁን እየተደረጉ ባሉት ጥረቶች መካከል የጎላ ክፍተት ይታያል።

ሆርን ሪቪው:

መንግሥት ወደፊት ሊደረግ በታቀደው ብሔራዊ ውይይት ምን የማሳካት ተስፋ አድርጎ ነው የተነሳው?

ይህ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይት በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ እንዲካሄድ ተስፋ እናደርጋለን። አንዳንድ አንኳር ልዩነቶቻችንን ለመፍታት ያለመ፣ በጥቂት የተመረጡ ልሂቃን የተባሉ ግለሰቦች መካከል በቻ የሚደረግ ውይይት ሳይሆን በዝቅተኛ ደረጃም ያሉትን የሕብረተሰብ ክፍሎችም የሚያሳትፍ ይሆናል። በህብረተሰባችን ውስጥ ብዙ የታመቁ ቅሬታዎች እንዳሉ ግልጽ ሲሆን፣ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳታቸው አይቀርም። የኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ፣ የተነሱ እና ከብዙ ጊዜ በፊት ተነስተው ሲንከባለሉ የቆዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሙሉ ጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸው ወደ አንድ ስምምነት መድረስ አለብን።

የእኛ ዋና አላማ ህብረተሰባችንን በግጭት አዙሪት ውስጥ ከትቶ እና የወደፊት ግስጋሴውን አደናቅፎ የረዥም ጊዜ፣ አንዳንዴም ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠሩ አለመግባባቶችን ማስወገድ ነው። ይህ አገራዊ ውይይት በጋራ መግባባት ላይ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁት እንዲህ ካለው ሁሉን አሳታፊ ውይይት ግብ ጋር የማይጣጣም ተቃራኒ ዓላማ ስላላቸው በዚህ ውይይት ውስጥ  እንደማይሳተፉ ደግሜ ላረጋግጥ  እወዳለሁ።

ሆርን ሪቪው፡-

ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተርባይን ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን በቅርቡ ከተሰማ በኋላ የመንግስት ቀጣይ እቅዶች ምንድን ናቸው ከዚህ አንፃር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገውን የሶስትዮሽ ድርድር በተመለከተ የኢትዮጵያ አቋም ምን ይመስላል?

ዲፕሎማት እንደመሆኔ የፕሮጀክቱን ቴክኒካል ዝርዝሮች በሙሉ በውል አላውቅም። ነገር ግን የተርባይኖቹን ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን አረጋግጣለሁ እና ግድቡ በውስን ተርባይኖች  ሃይል ማመንጨት ይጀምራል። ይህ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሁሉም የኢትዮጵያ ወዳጆች ትልቅ ስኬት ነው።

እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2011 የህዳሴው ግድብ ሲጀመር ኢትዮጵያ ምን አላማ እንዳላት ግልፅ አድርጋለች፡ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ መሰረታዊ የመብራት ተጠቃሚነትን ያጣች እና በጨለማ ውስጥ ለሚኖረው 70 በመቶ ለሚጠጋው ህዝቧ ሃይል ለማቅረብ ትፈልጋለች፡፡ እኔ ደግሜ መናገር የምፈልገው ኢትዮጵያ የታችኞቹን ተፋሰሶች ማለትም ግብፅና ሱዳንን ለመጉዳት ምንም አላማ እንደሌላት ነው። አባይ ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ስለሆነ እኛ የምንፈልገው ይህ ፕሮጀክት የትብብር ምንጭ እንዲሆን እንጂ የግጭት ወይም የንትርክ ምንጭ ሊሆን አይገባም። ይህ ደግሞ በህዳሴው ላይ ካለን አቋም ጋር ብቻ ሳይሆን ለላቀ ቀጠናዊ ቅርርብ እና ትስስር ካለን ራዕይ ጋር የሚጣጣም ነው።

የግንባታው ሂደት የግንባታ እና የዉሀ ሙሌት ሂደቶች በቅደም ተከተል የተነደፉ ናቸው-እያንዳንዱ እርምጃ በቀድሞው ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የውኃ ማጠራቀሚያ መሙላት ደረጃዎች በግንባታው ሂደት አመንክኖአዊ ቅደም ተከተል ውስጥ አንድ ደረጃ ብቻ ነው፡፡ ኤክስፐርት ወይም ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች የላይ ላይ  ትንተናቸው እነዚህን ሁለት ደረጃዎች እንደ ተለያዩ ሂደቶች የሚያቀርቡ አሉ፡፡ በተለይም ከውሀ ሙሌቱ  ሂደት አንጻር በዚህ ረገድ የህዳሴ ግድቡ እንዳይቀጥል ከሚከለክሉ ወገኖች ጋራ ምንም ዓይነት ግልጽም ሆነ የተሰወረ ስምምነት የለም፡፡  – በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን ድርድር በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ለሚደረገው የሶስትዮሽ ውይይት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች፡፡ እኔ እንደማውቀው፣ እየተካሄደ ያለው ሂደት በሁለት ምክንያቶች ለጊዜው ተቋርጧል፡አንደኛ፡ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ፕሬዝዳንት ክቡር ኤች.ኢ. ፊሊክስ – አንትዋን ቲሺሴኬዲ ወደ ሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ስለተዛወረ። የህዳሴው ውይይት በአዲሱ ሊቀ መንበር ስር በቀድሞው ሊቀመንበር ዘመን የተመዘገቡትን መልካም ውጤቶች እንደሚያጎለብት ተስፋ እናደርጋለን። በሁለተኛ ደረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በሱዳን እየታየ ያለው አለመረጋጋት ለህዳሴው ድርድሩ ጊዜያዊ መቋረጡ ሌላው ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ፈጣን መረጋጋት እና መደበኛ ሕይወት እንደሚቀጥል ተስፋ አላት፤ እንዲሁም አንዴ ሂደቱ ከቀጠለ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ወደፊት ለመሄድ ታስባለች። በቅርቡ በተደረጉ ውይይቶች፡ ተደራዳሪ አጋሮቻችን እንደፈለጉ ወጣ ገባ እንደማይሉ ተመልክተናል፣ አንድ የተሟላና ሁሉንም የሚያግባባ ሰነድ ላይ እስክንደርስ ድረስ በቅን ልቦና እንደሚደራደሩ ተስፋ እናደርጋለን። እንደምንም ብለን ልንቋቋማቸው የቻልናቸው ቴክኒካል ጉዳዮች አሉ፣ ነገር ግን እስካሁን ልንፈታ ያልናቸው አንዳንድ የህግ ጉዳዮች አሉ። በተመሳሳይ መልኩ ክፍተቶቹን ማጥበብ እና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መፍትሄ እንደምናገኝ እተማመናለሁ።

ሆርን ሪቪው፡-

ወቅታዊውንየኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል? የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ከሱዳን በኩል የአቋም ለውጥ ይኖራል ብሎ ይገምታል?

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የረጅም ጊዜ የጋራ መደጋገፍ ታሪክ አላቸው።

በቅርቡ፣ የኛ ጠቅላይ ሚኒስትር በፖለቲካ ልሂቃን እርቅ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምስረታ ላይ በጥረታቸው ያሳኩትን እናስታውሳለን፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን ችግር ሲገጥማቸው ከሱዳን ጎረቤቶቻቸው ልባዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ይህ የሱዳን አመራር በውጫዊ ሁኔታዎችም ሆነ በተጽእኖ አምጪ አካላት ምክንያት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት የደፈረበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡  ለዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ አፋጣኝ እልባት ለመስጠት በነባር ቀጠናዊ ዘዴዎች ማለትም በኢጋድ አማካኝነት ትቀጥላለች።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚመለከት ህዝቦቻችን በጋራ በመሥራት ብዙ መማርና ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ለዚህም ነው በአሁኑ ወታደራዊ ገዥዎች የተፈጠረው ከሱዳን ጋር ያለን ግንኙነት ያለፈ ታሪካችንን ያላገናዘበ እና ወደፊት ልናጎለብተው የምንችለውን አቅም አይመጥንም የምንለው፡፡

ሆርን ሪቪው፡

ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የወደፊቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

ብዙዎቹ ግቦቻችን እርስ በርስ የተያያዙ በመሆናቸው አንድን የውጭ ፖሊሲ ዓላማ፣ ለይቶ እንደ አንድ ግብ መነጠል አስቸጋሪ ነው። በአጠቃላይ ለመናገር፣ በ2022 ቀዳሚ ግባችን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋራ በቅርበት መሥራት ነው። የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋራ በቅርበት መሥራት  የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ተሳትፎ እና የረጅም ጊዜ አጋርነቶችን እና የልማት ፕሮጀክቶችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመፍጠር ያለንን ፍላጎት ያመላክታል። የሀገሪቱን የተለያዩ ፍላጎቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ልባችንን ከፍተን ከጥርጣሬና ፍረጃ ጸድተን ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በሙሉ ልብ ለመሥራት አቅደናል።

አሁን ካለው የግጭት ሁኔታ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ለአጋሮቻችን መሬት ላይ ያሉትን እውነታዎች እና ቀጣይ ለውጦችን ማሳወቅ ትቀጥላለች። ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በምናደርገው ጥረት እንዱ ምሰሶ መልሶ ግንባታ ነው፡፡ ስለዚህም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ለዚህም አጋሮቻችን እና ወዳጆቻችን መልሶ በመገንባት፣ በማስተካከል እና በጣም አስፈላጊ የሆነውን መደበኛ እና ሰላማዊ ሁኔታን ለማምጣት በምናደርገው ጥረት እንዲረዱን እንጠይቃለን።

 

ትርጉም በ ፍፁም ጌታቸው

Share